የኢትዮጵያ ሀይቆች ሞት / Eutrophication

በፋሲል ፀጋዬ

የውኃ አካላት ሞት/ Eutrophication, ሀይቆች ኩሬዎችና ሌሎች የውኃ አካላት ውስጥ ንጥረ ነገሮች (nutrients) ወይም ማዳበሪያ በሚበዛበት ወቅት የሚፈጠር የተፈጥሮ ሂደት ነው፡፡ ከየመፀዳጃ ቤት የሚወጣ ፍሳሽ፣ የእንሥሣት አዛባ፣ ከማሣዎች በጎርፍ እየታጠበ ወደ ሀይቆች የሚገባው የተፈጥሮም ሆነ ሠው ሠራሽ ማዳበሪያ በውኃ አካላቱ ውስጥ ያለመጠን በሚበዛበት ወቅት:- አልጌ፣ ተንሣፋፊ የውኃ ውስጥ አረሞቸ በብዛት እንዲያድጉ ያደርጋል፡፡ ምግብ እንደልብ በመገኘቱ ምክንያት የውኃ ውስጥ ትላትሎች  እና ነፍሳት ያለ ልክ ይራባሉ፣ የዓሣ ምርትም ለተወሠነ ጊዜ እየበዛ ይሄዳል ሆኖም በዛ መጠን አይቀጥልም፡፡

 የውኃ ውስጥ ነፍሣትና አረም በተፈጥሮ ሂደት ያድጋሉ፣ ይሞታሉ እንዲሁም ይበሰብሳሉ፣ የውኃውንም የምግብ ይዘት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ከበፊቱ የበዛ አልጌና አረም እንዲያድግ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ሰፊ ቦታዎችንም እየሸፈነ እንዲሄድ ያደርጋል፡፡ ይህ ድግግሞሽ ሲቀጥል ሃይቆች በውኃው ውስጥ ያለመጠን ለበዛው ነፍሳት ሁሉ ንጹሕ አየር ማቅረብ ያቅታቸዋል፡፡ በውኃው ውስጥ ያለው ኦክስጅን (O2) ይቀንሳል በተቃራኒው ጥቅም ላይ የዋለው ካርቦን ዳይ ኦክሣይድ(CO2) እና ሌሎች ጋዞች ይጨምራሉ፣ የውኃው ውሥጥ ሙቀት ከወትሮው በተለየ ከፍ ይላል፡፡ እጅግ የበዙት ነፍሳትና ዓሣዎችም በመታፈናቸው ምክንያት ይሞታሉ አንዳንዶቹም ዝርያቸው ይጠፋል:: አዲሱን ለውጥ መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎች በከፍተኛ ፍጠነት ይራባሉ:: ይህ ሌላ ዙር፣ ብዛትና ሞት ተከታታይ ሂደት ይፈጥራል፣ ውኃው መሽተት ይጀምራል፣ የውኃ ውስጥ አረም ከዳር በመጀመር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሥፋፋ ሰፊ ቦታዎችን በመሸፈን ማዕበልን ጨምሮ  የውኃውን የተፈጥሮ እንቅስቃሴ በማወክ ውኃው ራሱን እንዳያድስ ያደርጋል፡፡ 

ከውጭ በሚገባውም ሆነ ከውስጥ በበቀሉት አረምና ነፍሳት ሞት ምክንያት የበለፀገ ብስባሽ/ማዳበሪያ መጨመር ቋሚ ተክሎች እነዲያድጉ ያደርጋል፣ ከዳር የጀመረው ሂደት በዓመታት መካከል እየተስፋፋ አዳዲስ ረግረጋማ መሬት ብሎም መስክ በመፍጠር የውኃውን መጠን ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሠ እዲሄድ በማድረግ ሀይቁ ሙሉ ለሙሉ እዲደርቅ/እንዲጠፋ  ያደርጋል፡፡ ይህ ሂደት ነው እንግዲህ በሣይንሣዊ አጠራሩ ‘ዩትሮፊኬአሽን’/Eutrophication እየተባለ የሚጠራው፡፡    

lake-hawassa-1212

ስዕል 1፡ የሀዋሳ ሀይቅ የመጥፋት ሂደት፣ ፎቶ በፋሲል ፀጋዬ ጥቅምት 2009 ዓ.ም

 የደለል ክምችትና ከውኃ አጠቃቀም ጋር ተያያዥ የሆኑ ተጨማሪ ምክንያቶች ቢኖሩም በዚህ ሂደት ከጠፉ የሀገራችን የውኃ አካላት መካከል ታዋቂው የሀሮማያ ሀይቅ፣ ጅማ ከተማ አካባቢ የነበረው ቦይ ኩሬ በርካታ ጥናት የተደረገባቸውና ሌሎችም በአካል የሚታወቁ ናቸው፡፡ ውቢቷ  ሀዋሣ  ተገን አድርጋ የተቆረቆረችበት የሀዋሣ ሀይቅም ይህ አደጋ ካንዣበበባቻው የሥምጥ ሸለቆ ሀይቆች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች እነደሚሉት የሀዋሣ ሀይቅ በጣት ከሚቆጠር ዓመታት የዘለለ እድሜ እንደማይኖረው ተንብየዋል፡፡ የሀገር ኩራት የሆነው ውቡና ታላቁ የጣና ሀይቅም ቢሆን የችግሩ ውጤት እየታየበት ነው፡፡ በሠሜን እና ደቡብ ጎንደር አጎራባች ወረዳወች በአካባቢው አጠራር እንቦጭ (water hyacinth) እየተባለ የሚጠራውን አደገኛ የውኃ ውስጥ አረም በሰው ጉልበት ለማጸዳት እየተደረገ ያለ ጥረት ቢኖርም ችግሩ አረሙን በማጽዳት ብቻ የሚፈታ አይደለም፣ ወደ ሀይቁ የሚገባውን ደለልና ማዳበሪያ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ጭምር ማድረግ  ያስፈልጋል፡፡

እንግዲህ የሀገራችን ውብ ከተሞች ባህርዳርን ያለ ጣና፣ ሀዋሳን ያለ ሀዋሣ ሀይቅ፣ አርባምንጨን ያለ አባያና ጫሞ ማየት አይደለም ማሠብ ይከብዳል፡፡ ሞታቸውን እያፋጠነ ያለው ዩትሮፊኬሽን ነው፡፡ እያንዳንዱን ሀይቅ በዝርዝር በማጥናትና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ዘላቂ ሥራ መስራት ያሻል፡፡

ሂደቱን በአፋጣኝ ለማስቆም፡-

  • አረሙን በጀልባ ላይ በሚገጠም ማረሚያ (መጋፈፊያ) ማሽን በመጠቀም የውኃ ላይ አረሙን ማጽዳትና ለእንሰሳት መኖ በማቀነባበር የገቢ ምንጭ እንዲሆን ማድረግም ይቻላል፡፡
  • በምንም አይነት ሁኔታ የከተማ ፍሻሽ፣ የጎርፍ ውኃን ጨምሮ ወደ ሀይቁ እንዳይገባ ማድረግ፡፡
  • እነደየ ሀይቁ አቀማመጥና ተፋሰስ ጊዜያዊ የማብላያ ኩሬ/ግድብ መገንባትና ፍሳሽና ጎረፉ፣ ደለሉን ጥሎ እና የተፈጥሮ ሂደቱን ጨርሶ የጠለለውን ውኃ ብቻ ወደ ሀይቁ እንዲገባ ማድረግ፡፡
  • ዘላቂ የአፈር እቀባ ስራ መስራት፣ ልቅ ግጦሽን በማስቀረት በተፋሰሱ ውስጥ የደንና የሳር ሽፋን እነዲጨምር ማድረግ ዋና ዋና የመፍትሄ እርምጃዎች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሀይቆች የዓሣ ምርት የምናገኝባቸው፣ ዋነኛ የመዝናኛና የቱሪስት መስህብ ናቸው፡፡ የውኃ አካላት በየአካባቢው  በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሡ ለመሆኑ ለማንኛውም አስተዋይ ሠው ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም አፋጣኝ እርምጃ መወሠድ  አለበት፡፡ ውኃ የሚርቀን፣ መለወጥ በምንችለው ችግር  እጃችንን አጣጥፈን የምናይ አላዋቂ  ሕዝቦች መሆን ያለብን አይመስለኝም፡፡

አሁን ያለው ሁኔታ ተለውጦ ሀይቆቻችን የጠራ ሠማይን የሚያንጸባርቁ፣ ማእበል በየአለቶቻቸውና አሸዋማ ዳርቻዎቻቸው አረፋ የሚደፍቁበት፣ እስከነ ግርማ ሞገሣቸው ህጻናት የሚበርቁባቸው፣ ወራዙት የሚወዳደሩባቸው፣ ጎልማሶች የሚመሰጡባቸው፣ አረጋውያን ትዝታዎቻቸውን የሚጨዋወቱባቸው፣ የልባችን ሀሴት የሥልጣኔያችን ማሣያ እንደሚሆኑ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ 

lake-hik

ስዕል 2፡ ሀይቅ እስጢፋኖስ፣ ደቡብ ወሎ፣ ፎቶ በፋሲል ፀጋዬ

awash-eutrophication-1212

 ስዕል 3፡ አዋሽ ፣ ቆቃ፣ ምስራቅ  ሸዋ፣ ፎቶ በፋሲል ፀጋዬ

One thought on “የኢትዮጵያ ሀይቆች ሞት / Eutrophication

  1. Abnet says:

    Thank you Nitsuh Ethiopia, this is our priority, we have to awake and work hard to reverse the growing challeng. Water is life,
    Abenet,

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may also like

No announcement available or all announcement expired.