የአደስ አበባ መንገድ አስተናባሪዎች /Street Facilitators of Addis Ababa

በፋሲል ፀጋ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባችን ከያቅጣጫው የሚተመውን ህዝብና ተሽከርካሪ ለማስተላለፍ  ወጣት አስተናባሪዎች በዋና ዋና አደባባዮችና የባቡር መሻገሪያዎች ላይ ተመድበው ሢሰሩ ይታያሉ፡፡

ወጣቶቹ እያበረከቱ ያሉት አገልግሎት ለእግረኞችም ሆነ ለአሽከርካሪዎች  መልካም ነው፡፡ ሀሣቡን ያመጡቱም ሆነ ተግባራዊ ያደረጉትን ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ሊመሠገኑና ሊደነቁ ይገባል፡፡ እግረኞችም ሆን አሽከርካሪዎች እንዚህ ቆመው የሚያስተናግዱንን ወጣቶች በመታዘዝ ክብርና ድጋፍ ልንሠጣቸው ይገባል፡፡ እንዲያ ሲሆን ወጣቶቹ  ሥራቸውን ወደውና አክብረው ያስተናግዱናል፡፡

በተጨማሪም እነደዚህ ለሚያገለገሉን ወጣቶች ጤናና የወደፉት ሕይወት አብሮ መታሠብ አለበት፣ በማንኛውም የአገልግሎት መስክ በምስኪኖች ህልውና ላይ ምቾታችንን መገንባት ከሞራል ብቻ ሣይሆን ሀላፊነትን ከመወጣትና ከዘላቂነት አንፃር  መሠረት የለውም፡፡ ወጣቶች እኛን በማገልገል ለረዥም ሠዓት በተጨናነቀ ጎዳና ሲውሉ ለበርካታ አይነት መርዛማ የመኪና ጭስ ይጋለጣሉ፡፡ በተበከለ ከተማ መኖር በርካታ ሲጋራዎችን ከማጨስ በላይ ጉዳቱ የከፋ ነው ለምሳሌ የቻይናዋን  ዋና ከተማ የቤጅንግን አይር መተንፍስ በቀን 40 ሲጋራ የማጨስ ያክል ጉደት ይኖረዋል፡፡

በአጠቃላይ ረዥም ጎዳና ላይ የሚውሉ ወጣቶች የሚከተሉት የጤና ችግሮችና ጉዳቶች ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ከያንዳንዱ ጉዳት ሥር የመፍትሄ ሀሣቦችን አካትተናል፣ አንብበው አስተያየት ይስጡን፡፡

 1. ጎዳና ላይ ቆመው ሲውሉ በከፍተኛ ደረጃ ለመርዛማ የመኪና ጭሥ እንደሚጋለጡ ግልጽ ነው በመሆኑም፡-
 • ሰውነታተው የተለያየ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ማሶገድ ይችል ዘንድ ከግማሽ ሊትር ያላነሠ ወተት በቀን እነዲጠጡ ቢመቻችላቸው መልካም ነው፡፡
 • ቢያንስ በዓይን፣ በአፍና በአፍንጫ በቀጥታ የሚገባውን የመኪና ጭስ ለመከላከል ለዚሁ የተሰሩ ማስኮችና መነጽሮች በተወሰነ የጊዜ ገደብ ቢታደላቸውና ሥራ ላይ በሚሆኑበት ጊዜ ሁሉ እንዲጠቀሙበት ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ፡፡
 • ረዘም ላለ ጊዜ ቆመው በሥራታቸው ምክንያት የማህጸን ችግር እንዳያጋጥማቸው ፣ ከመርዛማ ጭስ የተነሳ ከፅንስ ጋር በተያያዘ ለሚወልዱት ልጅ አደጋኛ እንዳይሆን ሴቶች በዚህ ሥራ እነዳይሣተፉ ቢደረግ፡፡ ፍላጎቱ ላላቸው ሴቶች ሌላ ተመሣሣይ አገልግሎት እንዲሳተፉ ቢመቻች መልካም ነው፡፡
 • በዚህ አገልግሎት የሚሣተፉ ወጣቶችን ቁጥር ከፍ በማድረግ ቶሎ ቶሎ በሚቀያየር ፈረቃ እንዲሰሩ በማድረግ በመንገድ ላይ የሚቆዩበትን ጊዜ መቀነስ ፡፡
 • ተተኪዎችን በብዛት በማሣተፍ አንድ ሠው በዚሁ የማስተናበር ሥራ ከአንድ ዓመት በላይ እንዳይሠራ ማድረግ፡፡ሌሎች የሕዝብ አገልግሎት መስጫ መስኮችን በመክፈት ካንዱ ውደ አንዱ የሚሸጋገሩበትንና ቋሚ የሥራ እድል የሚያገኙበትን አሠራር ማመቻቸት፡፡
 1. ወጣቶቹ ቆመው ሲያስተናግዱን ያደረጓቸውን ጫማ ስናይ አንዳንዱ በነጠላ ጫም አንዳንዶቹ ደግሞ የማይመቸ ወይም ጠባብ ጫማ ተጫምተው ይታያሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ለዘላቂ የእግርና የወገብ ህመም እንዳያጋልጣቸው ደረጃውን የጠበቁ ረዘም ላለ ጊዜ ቆሞ ለመስራት የሚመች ጫማ በበጀት በመግዛት አለያም የተለያዩ በጎ አድራጊ አካላትን በማስተባበር እንዲሠጣቸው ቢደረግ፡፡
 2. ሁኔታውን ለመረዳት ትንሽ ደቂቃ ቆም ባልን ጊዜ የምናስተውለው የአንዳነድ ሰው ምግባር የሚገርም ነው፡፡ አንዳንዱ ጥሶ ለመሄድ ይታገላል፣ አንዳንዱ ትንሽ ሰከንድ ለምን ቆምን ብሎ ይበሣጭባቸዋል፣ አንዳንዱ አሽከርካሪ ፍሬን መያዝ ታክቶት በመጣበት ፍጥነት ለማለፍ ይሞክራል፣  አንዳንዱ ጆሮ በሚበጥስ ጥሩንባ ቀልባቸውን ይገፋል፡፡
 • ስርዓተ አልበኛውን የሚያስታግስና የሚቀጣ የትራፊክ ፖሊስና ጸጥታ አስከባሪ በአካበቢያቸው በማንኛውም ጊዜ ቢኖር፡፡
 • ህዝቡ እነዲተባበራቸውና እነዲታዘዛቸው በመገኛኛ ብዙሀን የማስተዋወቅና የማስተማስር ሥራ ቢሠራ፡፡ ስርዓት ባለው መልኩ ቢንቀሣቀሥ ደህንነትና ምቾት ለራሡ መሆኑን እነዲረዳው ማድረግ ናቸው፡፡
 • ሰውን ከአደጋ ለመጠበቅ ቢሰሩም እነሱ አደጋ ላይ እንዳይወድቁ፣ በአንዳንድ ቀዥቃዣ ወይም ለማጅ አሽከርካሪዎች ጉዳት ቢደርስባቸው በሥራ ላይ ያሉ ዜጎችን መጉዳት የተለየ የህግ ማእቀፍና የኢንሹራነስ አገልግሎት እዲያገኙ ቢደረግ፡፡

ከላይ የቀረቡት አስተያየቶችና የመፍትሄ ሀሣቦች በሙሉ የትራፍክ ፖሊሶችንና መንገድ በማጽዳት ሥራ ላይ የተሰማሩ   በአጠቃላይ ለማህበረሰቡ የመንገድ ላይ አገልግሎት የሚሰጡ ሌሎች ሠራተኞችን ጭምር ይመለከታል፡፡

የከተማ ኑሮ ሥርዓት ያስፈልገዋል፣ እነደዚህ መልክ የሚያሲዙ፣ የሚመክሩ፣ የሚገስጹ፣ የሚረዱ፣ የሚቆጣጠሩ፣ አስተናባሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ከተሜነት የከተማው ነዋሪዎች የሚስማሙበት፣ በአንድነት የሚገዙለት ሥርዓት፣ መተሳሰብና  የሰለጠነ ሰው ልማድ ነው፡፡ ከተማ የፈለጉትን  በዘፈቀደ የሚፈጽሙበት የሠዎች በረት አይደለም፡፡

ቸር ይግጠመን!

 For further reading you can visit the link about Beijing air pollution:

http://www.dailymail.co.uk/sciencetech/article-3201954/Breathing-Beijing-s-air-equivalent-smoking-FORTY-cigarettes-day-Smog-map-China-reveals-shocking-extent-pollution.html

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may also like

No announcement available or all announcement expired.